በወጣው ደንብ መሰረትም የሚከናወኑ ግንባታዎች በ30 ሜትርና ከዚያ በላይ ስፋት ካላቸው የዋና ዋና አውራ መንገዶች ቢያንስ 5 ሜትር ርቀው መከናወን አለባቸው።
ከ20 እስከ 30 ሜትር ስፋት ካላቸው የሁለተኛ ደረጃ መንገዶች ቢያንስ 4 ሜትር ርቀት እንዲሁም ከ15 እስከ 20 ሜትር ስፋት ካለው የሰብሳቢ መንገድ ቢያንስ 3 ሜትር ርቀት መጠበቅ እንዳለባቸው ያስቀምጣል።
ከዚህ በተጨማሪም ከ6 እስከ 15 ሜትር ስፋት ካለው የውስጥ ለውስጥ መንገድ ቢያንስ 2 ሜትር ያህል ርቀት መጠበቅ እንደሚገባ ያስገድዳል።
በዚህም ርቀታቸው በተወሰኑ ቦታዎች ውስጥ ከመንገድ እና ተያያዥ መሰረተ ልማቶች ውጭ ምንም ዓይነት ግንባታ ማከናወን ተከልክሏል፡፡
በተከለከለ ይዞታ ውስጥ ግንባታ ሲያከናውን የተገኘ ማንኛውም ሰው ወዲያውኑ እንዲያነሳ ይደረጋል፣ ተገቢው መቀጮ በመክፈል ተጠያቂም ይሆናል።
ስለሆነም በልማት ኮሪደሩ ውስጥ ከግንባታ እና ከመንገድ መካከል ርቀት እንዲጠብቅ በተደረገው ክልል ውስጥ ማንኛውንም ዓይነት ግንባታ ማከናወንም ሆነ እግረኛን መንቀሳቀስ የሚከለክሉ ተቀማጮችን ማኖር የተከለከለ ነው።
ማንኛውም አልሚ ከግንባታው እና ከመንገድ መካከል ርቀት እንዲጠብቅ በተደረገው ክልል ውስጥ የእግረኛ መንገድ ጌጠኛ ንጣፍ፣ አረንጓዴ ልማት እና ጌጠኛ መብራቶችን በራሱ ወጪ አልምቶ እንዲንከባከብ እና ጥበቃ እንዲያደርግ ኃላፊነት የተሰጠ ሲሆን የባነር፣ የጨርቅ፣ በሸራና በብረት ቋሚ የሚለጠፉ ማስታወቂያዎችን ሙሉ በሙሉ እንዲያነሳ ይገደዳል።
ማንኛውም አልሚ የህንፃውን ፅዳትና ንፅህና መጠበቅ፣ በአረንጓዴ ተክል እና ጌጠኛ መብራት ማስዋብ፣ ህንፃውን በባለሥልጣኑ በሚሰጥ የቀለም ምርጫና የመብራት ዓይነት ማሸብረቅ እና መቀባት፣ የህንፃውን ማስታወቂያዎች በኤሌክትሮኒክ ቴክኖሎጂ ብቻ በመጠቀም ተግባራዊ ማድረግ አለበት።
ሆኖም አልሚዎች በህንፃ ቀለም ፈንታ በሌላ የግንባታ ማጠናቀቂያ ቁስ ማለትም እንደ ፐርኬ፣ ከርቴን ዎል እና ክላዲንግ የተገነቡትን ባለሥልጣኑ እንደ ኮሪደሩ አካባቢ በሚወሰነው መሰረት ተነስቶ እንዲቀየር ሊያዝ ይችላል።
ለተግባራዊነቱ ክትትል የሚደረግ ሲሆን እንደ አስፈላጊነቱም እርምጃ የሚወሰድ ይሆናል።