በሀረሪ ክልል በክረምት በጎ ፈቃድ ከ114 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ስራ ተከናውኗል- አቶ ጌቱ ወዬሳ

በሀረሪ ክልል ባለፉት ሶስት ወራት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኘውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ያደረገና ከ114 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የበጎ ፍቃድ ስራዎች መከናወኑን የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ፅ/ቤት ሃላፊ አቶ ጌቱ ወዬሳ ገለፁ።

ኃላፊው ባለፉት ሶስት ወራት የተከናወኑ የክረምት በጎ ፍቃድ ስራዎች በሚመለከት እንደተናገሩት በክልሉ በበጎ ፍቃድ የሚከናወኑ ስራዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበተ ይገኛል።

የሚከናወኑ ስራዎችም በተለይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኘውን የማህበረሰብ ክፍል ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚህም ባለፉት ሶስት ወራት በተከናወነ የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ከ114 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመትና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኘውን የማህበረሰብ ክፍል ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎች መከናወናቸውን አብራርተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በክረምቱ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ በ14 የተለያዩ ዘርፎች ውጤታማ ስራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን ጠቁመዋል።

በተለይም በክልሉ ከተማና ገጠር ወረዳዎች የበርካቶችን ቤት በማደስ የአቅመ ደካማ ወገኖችን መሰረታዊ ችግር መቅረፍ ተችሏል ብለዋል።

በቤት እድሳትና ግንባታ መርሃግብሩ የተለያዩ የመንግስት ተቋማት፣ ባለሃብቶች፣ የሀይማኖት ተቋማትና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ 129 ቤቶችን ለማደስና ለመገንባት ታቅዶ በእስካሁኑ 74 ቤቶች ተጠናቀው ለተጠቃሚው መተላለፋቸውን አስረድተዋል።

ቀሪ ቤቶችን አጠናቆ ለተጠቃሚው ለማስተላለም ርብርብ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል

ከዚህ በተጨማሪም ከ6ሺህ በላይ ለሚሆኑ የአቅመ ደካማ ቤተሰብ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ ተማሪዎች በኢኮኖሚ ውስንነት ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው እንዳይርቁ ማድረግ ስለመቻሉ ጠቅሰዋል

ከዚህ ባለፈም በክረምቱ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የአካባቢን ሰላም በማስጠበቅ፣ በፅዳት፣ በአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር፣ በደም ልገሳ፣ በነጻ ህክምና አገልግሎት፣ የማጠናከሪያ ትምህርት እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች ላይም ውጤታማ ስራዎች መሰራታቸውን ነው ያብራሩት።

የተከናወኑ ስራዎችም የአመራሩ ቅንጅትና ቁርጠኝነት የታየበት፤ ስራዎች በአግባቡ ከተመሩ ስኬታማ የማይሆኑበት ምክንያት እንደሌለ የታየበትና ለቀጣይ ተልዕኮዎችም በተሞክሮነት የሚወሰዱ ግብዓቶች የተገኙበት ነው ብለዋል አቶ ጌቱ።

በቀጣይ መተባበራችንና በመደጋገፋችንን በማጠናከር አንዱ የሌላው ሸክም ሳይሆን ድጋፍና ምርኩዝ መሆኑን በተግባር ማረጋገጥና የሀገራችንን ብልፅግና ለማረጋገጥ መረባረብ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

Leave a Comment

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው

Scroll to Top