በሀረሪ ክልል የአከራይና ተከራይ ህጋዊ ውል ምዝገባ ከነገ ጀምሮ ይካሄዳል
በሀረሪ ክልል የአከራይና ተከራይ ህጋዊ ውል ምዝገባ ከነገ ረቡዕ ህዳር 11/2017 ዓ.ም ጀምሮ እንደሚካሄድ በክልሉ የመንግስት ቤቶች አስተዳደር ኤጀንሲ አስታወቀ።
በአዲሱ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥርና አስተዳደር አዋጅ 1320/2016 መሰረት በማድረግ የአከራይና ተከራይ ህጋዊ ውል ምዝገባ ከነገ ረብዕ ህዳር 11/2017 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ታህሳስ 10 ቀን 2017 ዓ.ም ለአንድ ወር እንደሚቆይ ተገልጿል።
በዚህም መሰረት ለምዝገባ ተከታዮቹ ሰነዶችና ሁኔታዎች እንደሚያስፈልጉ ተገልጿል:-
1) በህግ አግባብ የተዘጋጀ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ውል ሰነድ፣
2) የአከራይና ተከራይ የነዋሪነት መታወቂያ፣ የመስሪያ ቤት መታወቂያ፣ መንጃ ፍቃድ፣ ፓስፖርት፣ የጥብቅና ፍቃድ፣ የሠራተኞች ጡረታ መታወቂያ፣ የዩንቨርስቲ ወይም ኮሌጅ ተማሪ የታደሰ መታወቂያ ወይም የሙያ ሥራ ፍቃድ ኦርጅናልና ኮፒ፣
3) የመኖርያ ቤት ኪራይ ውሉ የሚመዘገበው በወኪል ከሆን ሕጋዊ ውክልና የሁለት ምስክሮች የታደሰ መታወቂያ ኦርጅናልና ኮፒ፣
4) አከራይ የመኖሪያ ቤቱን ለማከራየት የሚያስችል መብት እንዳለው የሚያሳይ ህጋዊ ሰነድ ማለትም:-
ሀ) የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ወይም
ለ) ሰነድ አልባ ይዞታዎች መሆኑን ከሚመለከተው አካል ማስረጃ ወይም
ሐ) በፍርድ አፈጻጸም የተሸጠ ንብረት ሰነድ ወይም
መ) የተከራየው ቤት በውርስ የተገኘ ሆኖ ስም ዝውውር ካልተፈፀመ የወራሽነት ማረጋገጫ
ኦርጂናልና ኮፒ ይዘው በአካል መቅረብ ያለባቸው መሆኑንና ምዝገባው በየወረዳው በሥራ ሰዓት እንደሚካሄድ ተገልጿል።
የመኖሪያ ቤት ኪራይ ውል ምዝገባ በተቀመጠው ጊዜ ውስጥ ያላከናወኑ አከራይ እና ተከራዮች በቅጣት ወደ ውል ሥርዓቱ እንዲገቡ የሚደረግ መሆኑ ተጠቁሟል።

All reactions: