በሀረር ከተማ ኢማም አህመድ አልጋዚ መስኪድ ተፈጥሮ የነበረው አለመግባባት በሰላማዊ መንገድ ተፈቷል- ሼክ አብዱሰላም ጂብሪል

ሀረር መስከረም 29/2017(ሀክመኮ):- በሀረር ከተማ ኢማም አህመድ አልጋዚ መስኪድ ተፈጥሮ የነበረው አለመግባባት በሰላማዊ መንገድ መፈታቱን የሀረሪ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼክ አብዱሰላም ጂብሪል አስታወቁ።

በሀረር ከተማ በተለምዶ አራተኛ መስጂድ ተብሎ በሚጠራው የኢማም አህመድ አልጋዚ መስጂድ ከሰሞኑን ተፈጥሮ የነበረው አለመግባባት በሰላማዊ መንገድ መፈታቱን የሀረሪ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።

መግለጫውን የሰጡት የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ሼክ አብዱሰላም ጂብሪል ሀረር በሰላም እና መቻቻል ከተማነት አለም አቀፍ ሽልማት እና እውቅናን ያገኘች ከተማ መሆኗን ጠቁመው የተፈጠረውን አለመግባባት በምክክር መፍታት መቻሉን ገልፀዋል።

አለመግባባቱ በተወሰኑ ግለሰቦች መካከል የነበረ መሆኑን በመጠቆም አንዳንድ ግለሰቦች የተፈጠረውን አለመግባባት ወደ ብሄር ፀብ ለማሳደግ ሙከራ ማድረጋቸውን ገልፀዋል።

በተለይ ማህበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም ብሄርን ከብሄር የሚያጋጩ የተሳሳቱ እና መሰረት የሌላቸው መረጃዎች በአንዳንድ ግለሰቦች ሲሰራጩ መስተዋላቸውን ጠቁመዋል።

ይሁን እንጂ ሀረር የተለያየ እምነት ፣ ባህል እና ቋንቋ ያላቸው ህዝቦች ለዘመናት በሰላም እና አብሮነት በፍቅር የኖሩባት እና እየኖሩባት የምትገኝ ከተማ ናት ብለዋል።

ይህም በህዝቦቿ መካከል ያለው ጠንካራ ማህበራዊ ትስስር አለመግባባቱን ወደከፋ ደረጃ ሳይስፋፋ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ማገዙን ገልፀዋል።

የምክር ቤቱ አመራሮች አለመግባባቱ ከተከሰተበት ግዜ ጀምሮ ከክልሉ መንግስት እና የፀጥታ ተቋማት ጋር በቅርበት በመወያየት ህዝቡን ባሳተፈ መልኩ ችግሩን ለመፍታት ሲሰራ መቆየቱን አስረድተዋል።

በዚህም በዛሬው ዕለት የፌዴራል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት አመራሮችን ጨምሮ የአካባቢው ማህበረሰብ በተገኘበት አለመግባባቱን የፈጠሩትን ግለሰቦች ከመስኪዱ አመራርነት እንዲነሱ መደረጉን አስታውቀዋል።

በተነሱት አመራሮች ምትክም 15 አዲስ እና ገለልተኛ የሆኑ አባላትን በውስጡ ያቀፈ ኮሚቴ መስኪዱን በበላይነት እንዲያስተዳድር መሰየሙን አስታውቀዋል።

የሀረሪ እና ኦሮሞ ህዝብ ለዘመናት በአብሮነት የኖሩ ታሪካዊ የሆነ በአንድ ላይ የተገመደ የማይለያይ ወንድማማች ህዝብ መሆኑንም ፕሬዝዳንቱ በመግለጫው ጠቁመዋል።

በመሆኑም ብሄርን ከብሄር ማጋጨት በእስልምና አሰተምህሮትም የተጠላ እና የተወገዘ እና ህዝበ ሙስሊሙ ባጠቃላይ ሊያወግዘው የሚገባ ተግባር መሆኑን አስገንዝበዋል።

ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት የሚንቀሳቀሱ አካላትን ከመንግስት ጋር በመሆን በህግ ተጠያቂ በማድረግ አደብ ለማስገዛት እንደሚሰራም ገልፀዋል።

ማህበረሰቡ ለዘመናት በአብሮነት እንዲኖር መሰረት የጣለውን ሰላም ዋጋ በመስጠት ለምዕመኑ በማስተማር ሰላሙን በባለቤትነት እንዲጠብቅ በማድረግ የሀይማኖት አባቶች ሀላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አስተላልፈዋል።

የክልሉ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ህዝበ ሙስሊሙን በዕኩልነት ለማገልገል የተቋቋመ ተቋም መሆኑን በማመላከት ከመንግስት ጋር በመሆን ህገ ወጥነትን ለመከላከል እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

በነገው ዕለትም አዲስ የተሰየመው ኮሚቴ የስራ ርክክብ እንደሚያደረግ ገልፀዋል።

May be an image of 1 person

All reactions:

26Shemshadin Abas Ibrosh, Nesru Ali and 24 others

Leave a Comment

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው

Scroll to Top