የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በክልሉ በ2017 በጀት ዓመት ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎችን በሚመለከት እንዳሉት የገቢ መሰረት በማስፋት ገቢን አሟጦ ለመሰብሰብ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ ገልፀዋል።
በክልሉ የቱሪዝም ልማት ስራዎች እንዲጠናከሩ ከፍተኛ ትኩረት ይሰጣል ብለዋል።
በጤና አገልግሎት፣ በትምህርት ጥራት ፣ እንዲሁም በግብርና ዘርፎ ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ ስራ በልዩ ትኩረት ይከናወናል ብለዋል።
በከተማው የተጀመረው የኮሪደር ልማት ስራ በያዝነው የበጀት አመት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
የኮሪደር ልማቱ የሥራ ባህልን የቀየረ ከመሆኑ ባሻገር የከተማዋን የዘመናት ችግር በአጭር ጊዜ ውስጥ እያቃለለ የመጣ በመሆኑ ተሞክሮውን በሌሎች ፕሮጀክቶች ለመድገም እንደሚሰራ ገልጸዋል።
የክልሉ መንግስት በሚያከናውናቸው የልማት ስራዎች ለስራ አጥ ወጣቶች ስራ እንዲፈጥሩ የማድረግ ተግባር ቀዳሚ የትኩረት አቅጣጫችን ሆኖ ይቀጥላል ብለዋል።
በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች እንዲሁም በሰው ተኮር ተግባራት በልዩ ትኩረት የሚሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
እንዲሁም ህገ ወጥ ግንባታና የመሬት ወረራ ላይ ሕግ ማስከበር ስራ ይሰራል ብለዋል።
የብልሹ አሰራርና ሌብነት ትግል ይበልጥ በማጠናከር የተጠያቂነት ስርዓቱን የማስፈና ስራም በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
ህብረተሰቡ የሚያነሳቸው የአገልግሎት አሰጣጥና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲሁም ብልሹ አሰራር ለመፍታትና ለማረም የተለያዩ የሪፎርም ተግባራት እንደሚያከወን ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።
የኑሮ ውድነት ጫናን ለመቀነስ በተለይ የመሰረታዊ የምግብ ሸቀጦች አቅርቦት ለማሳደግ የአቅርቦት ሰንሰለቱን በመቁረጥ ሸማቹን ከተጠቃሚው ጋር በማገናኘት ገበያን የማረጋጋት ስራዎች እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
እንዲሁም ሸቀጦች ላይ ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ አካላት ላይ የክትትልና ቁጥጥር ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
የክልሉን ሰላም ለማጠናከር፣ የህግ የበላይነት እንዲከበር የህዝቦችን የአብሮነት፣ የመቻቻል እሴት የማጎልበት ስራ የህልውና ጉዳይ አድርገን እንሰራለን ብለዋል።