በክልሉ እየተከናወኑ የሚገኙ የኮሪደር ልማት ስራዎች ግለታቸውን ጠብቀው እንዲቀጥሉ በትኩረት ይሰራል- አቶ ኦርዲን በድሪ

በክልሉ እየተከናወኑ የሚገኙ የኮሪደር ልማት ስራዎች ግለታቸውን ጠብቀው እንዲቀጥሉ በትኩረት ይሰራል- አቶ ኦርዲን በድሪ

ሀረር ጥቅምት 23/2017(ሀክመኮ):- በክልሉ እየተከናወኑ የሚገኙ ኮሪደር ልማት ስራዎች ግለታቸውን ጠብቀው እንዲቀጥሉ በትኩረት ይሰራል ሲሉ የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለፁ።

የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በከተማው የተመረጡ ኮሪደሮችን መልሶ ለማልማት በተዘጋጀ ዕቅድ ላይ ከካባኔያቸው እና የወረዳ አመራሮች ጋር መክረዋል።

የመልሶ ልማት ዕቅዱ በመድረኩ ላይ ቀርቦ ውይይት የተካሄደበት ሲሆን የኮሪደር ልማት ስራው ለማህበረሰቡ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጥ መሆኑን ርዕሰ መስተዳደሩ ገልፀዋል።

ካሁን ቀደም የተከናወኑ የኮሪደር ልማት ስራዎች ጠንክሮ መስራት ከተቻለ አገርን መቀየር እንደሚቻል በተግባር የተረጋገጠበት መሆኑንም አስገንዝበዋል።

የኮሪደር ልማት ስራ ዋና አላማ ምቹ የመኖሪያ አካባቢዎችን በመፍጠር የነዋሪዎችን የኑሮ ደረጃ ማሻሻል እና ዘላቂ አካባቢዎችን መፍጠር መሆኑንም አመላክተዋል።

የኮሪደር ልማት ስራው ከ1 ሺህ ዓመት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረችው ዕድሜ ጠገቧ ሀረር ከተማ የሚመጥናትን እድገት እውን ለማድረግ እያገዘ መሆኑን ተናግረዋል

በተለይ የከተማዋ ልማት በአገር አቀፍ ደረጃ ትኩረት ማግኘቱ ከተማዋን በሚፈለገው ልክ ለማሳደግ የተጀመረውን ጥረት የሚያግዝ ነው ብለዋል።

በሌላ በኩል በክልሉ በቀጣይ የኮሪደር የመልሶ ልማት ለማከናወን የተለዩ አካባቢዎችን በተመለከተ መንግስት ማህበረሰቡን የማፈናቀል ፍላጎት እንደሌለው ርዕሰ መስተዳድሩ ገልፀዋል።

መልሶ ልማት በሚከናወንባቸው አካባቢዎች ማህበረሰቡ ባለበት ቦታ ይዞታውን እንዲያለማ ቅድሚያ እንደሚሰጠው ጠቁመው ነዋሪውን ወደ ተቀያሪ ቦታ ማዛወር የመጨረሻ አማራጭ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በቀጣይ የሚከናወኑ የመልሶ ልማት ስራዎች ካሁን ቀደም ሲስተዋሉ የቆዩ የመንገድ፣ መናኸሪያ፣ ገበያ ስፍራ፣ የህዝብ መዝናኛ እና ሌሎች የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ የሚያደርጉ መሆናቸውንም ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቁመዋል።

በክልሉ እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ስራ ግለቱን ጠብቆ እንዲቀጥል በትኩረት እንደሚሰራም ገልፀዋል።

በየወረዳው የተመደቡ የካቢኔ አመራሮችም ለኮሪደር ልማት ስራው መፋጠን የጀመሩትን ድጋፍ እና ክትትል አጠናክረው እንዲቀጥሉ ርዕሰ መስተዳድሩ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።

All reactions:

66Eliyas Abdurhman, Hasan Adam and 64 others

Leave a Comment

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው

Scroll to Top