በክልሉ የሰፈነው አዎንታዊ ሰላምና ፀጥታ ለልማቱ ምቹ መደላድሎችን ፈጥሯል – አቶ ቶፊቅ መሀመድ

የሀረሪ ክልል ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ሃላፊ አቶ ቶፊቅ መሀመድ ከክልሉ ብዙሀን መገናኛ ኤጀንሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ ባለፉት አምስት የለውጥ አመታት ሰላም ወዳዱን የክልሉን ህዝብ ባሳተፈ መልኩ በተከናወኑ ተግባራት በክልሉ የተረጋጋና አዎንታዊ ሰላም ሊሰፍን መቻሉን ገልጸዋል።

ሀገራዊ ለውጡ ያልተዋጠላቸው አንዳንድ ፀረ-ሰላም ሀይሎች በመቻቻልና በፍቅር ለዘመናት በኖሩ ህዝቦች መካከል ጥላቻን በመዝራት በክልሉ ግጭትና አለመረጋጋት እንዲፈጠር ያደረጉ ሙከራዎችን ከሰላም ወዳዱ የክልሉ ህዝብ ጋር ሆኖ መመከት መቻሉንም አስታውሰዋል።

ባለፉት አምስት አመታት የክልሉን የፀጥታ ተቋማት በአዲስ መልክ በማደራጀትና በማጠናከር እንዲሁም የፖሊስና ሚሊሻ አባላትን አቅም በመገንባት የህዝብ ሰላምና የህግ የበላይነትን ለማስከበር የተሰጣቸውን ተልዕኮ በአግባቡ እንዲወጡ የሚያስችላቸውን ቁመና እንዲላበሱ የተሰሩ የለውጥ ስራዎች ውጤት ማምጣታቸውንም ገልፀዋል።

በአሁኑ ጊዜ በክልሉ የሰፈነው አዎንታዊ ሰላምና ፀጥታ በፀጥታ አካላት ጥረት ብቻ የመጣ አይደለም ያሉት አቶ ቶፊቅ የሰላም አደረጃጀቶች ሚናና የአመራሩ ቁርጠኝነት የአንበሳውን ድርሻ እንደሚይዝም አመልክተዋል።

ባለፉት አምስት የለውጥ አመታት የክልሉ ህዝቦች የሚታወቁበትን የሰላም፣ የፍቅር፣ የመቻቻልና የአብሮነት በጎ እሴቶችን በማፅናት የሰፈነው የተረጋጋ አዎንታዊ ሰላምና ፀጥታ ለልማቱ ምቹ መድላድሎችን የፈጠረ ስለመሆኑም ገልፀዋል።

አቶ ቶፊቅ አክለውም በአሁኑ ወቅት ክልሉ ለሌሎችም ክልሎች ማሳያ በሚሆን ደረጃ ሰላም የሰፈነበትና አንድም የፀጥታና የወንጀል ስጋት የሌለበት የልማት እንቅስቃሴ የሚስተዋልበት ክልል መፍጠር ተችሏል ብለዋል።

በክልሉ ለሰፈነው አዎንታዊ ሰላምና ፀጥታ የክልሉ ፖሊስና ሚሊሻ ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ ከአጎራባች ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የፀጥታ አካላትና ከህዝብ ጋር በጋራ በመሆን ላደረጉት ርብርብ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በቀጣይም በክልሉ የፀጥታ ተቋማት ግንባታ ተግባራት ላይ ትኩረት በማድረግ የተጀመሩ የለውጥና ሪፎርም ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ጨምረው ገልፀዋል።

በክልሉ የተገኘውን አዎንታዊ ሰላምና መረጋጋት አስጠብቆ በማፅናት ዘላቂ ለማድረግ የፀጥታ መዋቅሮች ከሰላም አደረጃጀቶች ጋር ተቀናጅተው እየሰሩ መሆኑንም አቶ ቶፊቅ ተናግረዋል።

ባለፉት አምስት የለውጥ አመታት በክልሉ ሰላምና ፀጥታን በማስፈን ረገድ የተገኙ ስኬቶችን ቀጣይነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።

May be an image of 1 person, dais and text

All reactions:

Leave a Comment

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው

Scroll to Top