ሀረር ሀምሌ 16/2016(ሀክመኮ):- በሀረሪ ክልል የ2016 በጀት አመት የመንግስት እና የፓርቲ ሥራዎች እቅድ አፈፃፀምና የ2017 እቅድ ዝግጅት ግምገማ መካሄድ ጀመረ
የሀረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወ/ሮ ሮዛ ኡመር በመድረኩ መክፈቻ ላይ እንደገለፁት መድረኩ በ2016 በጀት አመት የተሰሩ የመንግስትና የፓርቲ ስራዎች የሚገመገሙበት ነው።
በ2016 በጀት አመት ለመፈፀም ከታቀዱት የልማት፣ የመልካም አስተዳደር እና የሰላም ስራዎች አንፃር አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።


በቱሪዝም፣ በግብርና፣ በትምህርት፣ ጤና፣ በገቢ አሰባሰብ፣ በፕሮጀክቶች፣ የኑሮ ውድነት ጫናን በመቀነስ፣ በፅዳትና ውበት፣ በቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ እንዲሁም የክልሉን ዘላቂ ሰላም አስጠብቆ በመጓዝ በኩል ስኬታማ ስራዎች መከናወናቸውንም ገልጸዋል።
የግምገማ መድረኩ በበጀት ዓመቱ በተከናወኑ ተግባራት የነበሩ ክፍተቶችን በማረም ጠንካራ ጎኖችን አጠናክሮ ለማስቀጠል እና የ2017 የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ለመምከር የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።
የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌቱ ወዬሳ በበኩላቸው በ2016 በጀት አመት ለማሳካት በዕቅድ የተያዙ የተግባር አፈጻጸም ረገድ ከፍተኛ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል፡፡
አባልና አመራሩ በፓርቲው እሳቤዎችና አቋሞች ላይ የጠራ ግንዛቤና አመለካከት እንዲኖራቸው በማድረግ ረገድ ፓርቲው “ከዕዳ ወደ ምንዳ” በሚል ስያሜ በብሄራዊ ገዥ ትርክት እና ሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ የተሰጡ ስልጠናዎች ስኬታማ እንደነበሩ ጠቅሰዋል፡፡
በተጠናቀቀው የበጀት አመት የተከናወኑ ተግባራት በጊዜ እና ጥራት በመገምገም ለቀጣይ ተልዕኮ ዝግጅት የሚደረግበት መሆኑን ገልፀዋል።
ዛሬ የተጀመረው የግምገማ መድረክ እስከ ነገ ድረስ እንደሚቀጥል ከወጣው መርሃግብር ለማወቅ ተችላል።
በመድረኩ ላይም የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወ/ሮ ሮዛ ኡመር፣ የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌቱ ወዬሳን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም እስከ ወረዳ ያሉ የመንግስትና የፓርቲ አመራሮች እየተሳተፉ ነው።