ሀረር ነሀሴ 20/2016(ሀክመኮ):- በሀረሪ ክልል በኮሪደር ልማት ስራ የተመዘገቡ ውጤቶች በተሻለ ፍጥነት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ርብርብ እንደሚደረግ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለፁ።
የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ የሀረር ከተማን ስትራቴጂክ የልማት እቅድ ለመምራት ከተቋቋመው ግብረሃይል ጋር በከተማው እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎች ላይ መክረዋል።
በመድረኩም እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎችን በተመለከተ ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል።
ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ኦርዲን በድሪ በምክክሩ ላይ እንደገለፁት በክልሉ ገቢራዊ እየሆነ ያለው የኮሪደር ልማት ስራ የከተማዋን ገፅታ ከመቀየር ባለፈ ምቹ የእግረኛ መንገዶች እንዲኖር እያስቻለ ነው።
በተለይ በከተማ ውበት እና ፅዳት የተሰራው ስራ ከተማዋን ለኑሮ እና ስራ የተመቸች በማድረግ ረገድ አበረታች ውጤቶች ማስገኘቱን ተናግረዋል።
ከተማዋን በፕላን እና ስርዓት የምትመራ ለማድረግ ትኩረት መሰጠቱን የገለፁት ርዕሰ መስተዳድሩ የተከናወኑ የልማት ስራዎችን መንከባከብ እና መጠበቅ ይገባል ብለዋል።
በተለይ ጅምር የልማት ስራዎችን በጊዜ የለኝም መንፈስ በፍጥነትና ጥራት በማከናወን የማህበረሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ርብርብ እንደሚደረግ ገልፀዋል።
የመንገድ ዳር ንግድን ከመከላከል ስርዓት ከማስያዝ አንፃር የተጀመሩ ስራዎች ለማስቀጠል በቁርጠኝነት እንደሚሰራም አመላክተዋል ርዕሰ መስተዳድሩ።




