ሀረር ጥቅምት 8/2017(ሀክመኮ):- በየደረጃው ያለው አመራር የአገልጋይነት መንፈስን ተላብሶ የማህበረሰቡን ጥያቄ ለመመለስ ሊሰራ እንደሚገባ የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለፁ።
በሀረሪ ክልል “የህልም ጉልበት ለዕምርታዊ እድገት” በሚል መሪ ቃል ሲካሄድ የቆየው 2ኛው ዙር ብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ስልጠና በዛሬው ዕለት ተጠናቋል።
የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በስልጠናው መዝጊያ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለፁት በክልሉ በሁሉም ዘርፍ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን የማስፋት ስራ ይሰራል።
በተለይ ለወጣቶች እና ሴቶች የስራ ዕድል ፈጠራ በሁሉም ወረዳ እና ሴክተር መስሪያ ቤቶች ልዩ ትኩረት የሚሰጠው መሆኑን ገልፀዋል።
በሌላ በኩል ማህበረሰቡን እያስመረረ ያለውን የኑሮ ውድነት ጫና ለመቀነስ በክልሉ የተጀመረውን የቅዳሜ ገበያ ጅምር ስራ ለማስፋት ይሰራል ብለዋል።
የቅዳሜ ገበያው የታለመለትን አላማ እንዲያሳካ የደላሎችን ጣልቃ ገብነት በማስቀረት ሸማቹን ከአምራቹ ጋር በቀጥታ በማገናኘት ማህበረሰቡ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲሸም ለማስቻል ትኩረት ተሰጥቶት ይሰራል ሲሉ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል ማህበራዊ ልማቶች እና እሴትን በማጠናከር ረገድ የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ ክህሎቱ የዳበረና እውቀትን ያነገበ መልካም ስነ ምግባር ያለው ትውልድ ለመገንባት በትኩረት እንደሚሰራ ገልፀዋል።
ሀረር የዳበረ ማህበራዊ እሴት ያላት ከተማ መሆኗን የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ ቀድመው የነበሩ የህዝቦች አብሮነት፣ መቻቻል እና የሰላም እሴቶች ከበፊቱ በተሻለ እንዲጎለብቱ በማድረግ በክልሉ አዎንታዊ ሰላምን ለማረጋገጥ እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።
ሰላም በሌለበት የኢኮኖሚ ዕድገትም ሆነ ሌሎች ልማቶችን ዕውን ማድረግ አዳጋች በመሆኑ የህግ- የበላይነትን የማረጋገጥ ስራ የአመራሩ ቁልፍ ስራ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ለአገር ሰላም ጠንቅ የሆኑትን የሀይማኖት እና የብሄር ፅንፈኝነት አመለካከቶችን በተለይ በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ ሀሰተኛ እና ፀብ ቀስቃሽ መልዕክቶችን በማጥራት ፅንፈኞችን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ እንደሚሰራ ገልፀዋል።
አመራሩም ፅንፈኝነትን መታገል ቁልፍ ስራ መሆኑን ተገንዝቦ የሰላም አደረጃጀቶችን በማጠናከር ሀላፊነቱን እንዲወጣ አሳስበዋል።
በተለይ አመራሩ የአገልጋይነት መንፈስን ተላብሶ የማህበረሰቡን ጥያቄ ለመመለስ ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በተቋማት ዲጂታል አሰራሮችን ተግባራዊ በማድረግ ሌብነት እና ብልሹ አሰራሮችን መታገል እንደሚገባም ገልፀዋል።
የማህበረሰቡን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመቅረፍ ወረዳዎች የመልካም አስተዳደር ዕቅድ በማውጣት በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባም አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
የሪፎርም ስራዎች በክልሉ በላቀ ትኩረት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገልፀዋል።