ከሀረሪ ክልል የፀጥታ ምክር ቤ/ት የተሰጠ መግለጫ
የሀረሪ ክልል ፀጥታ ም/ቤት ወቅታዊ ክልላዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል:-
ሠላም በሁላችንም እጅ ያለ ትልቅ ሀብት መሆኑን አውቀን በአግባቡ እንከባከበው እንጠቀምበት ።
የተከበራችሁ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ የክልላችን ነዋሪዎች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባ ገዳዎች የመንግስት ሠራተኞች፣ ምሁራን፣ አርሶ አደሮች፣ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት፣ ውድ ወጣቶች፣ በሀገር ውስጥም በውጭ ሀገር የምትገኙ የማህበረሰብ አንቂ አካላት፣ የፍትህና ፀጥታ አካላት እንደሚታወቀው የለውጡ መንግስታችን ሲንከባለሉ የቆዩ የኃይማኖት ነፃነት እና የእኩልነት ጥያቄዎችን ለመመለስ በአንድ በኩል የተለያዩ ማሻሻያዎችን እያደረገ በሌላ በኩል ለህዝቦች ሠላም እና የብልጽግና ጉዞ ለማሳካት በቁርጠኝነት እየሠራ ይገኛል።
በተለይ በክልላችን ለህዝብ ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት መንግስት ከህዝብ ጋር ተቀራርቦ እየተረባረበ መሆኑ ለሁላችንም ሀቅ የሆነ ጉዳይ ነው።
በዚህም ባሻገር በምእመናንና በህዝብ ዘንድ ምስክርነት የተሰጣቸው አበረታች ውጤቶች ተመዝገው የኃይማኖት ተቋማት በነፃነት እራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯዊ።
ሆኖም በአንዳንድ የእምነት ተቋማት የሚገኙ ግለሰቦች የግል ጥቅማና ፍላጎታቸውን ለማሳካት እምነት ተቋማት ስር ተሸሽገውና በቡድን ተካፋፍለው እና ልዩነታቸው ወደ ህዝቡ በማስገት ግጭት ለመፍጠር እንቅስቃሴ እያደረጉ ይገኛል።
መንግስት ፀጥታ እና ህግን ከማስከበር ባለፈ በኃይማኖት ተቋማት የውስጥ አሰራር ጣልቃ ባለመግባት እነዚህ አካላት ችግሮቻቸውን ከተቻለ በውይይት ካልተቻለ ደግሞ በህግ አግባብ እንዲፈቱ ከፍተኛ ጥረት ያደረገ ቢሆንም ግለሰቦቹ ለግል ጥቅማቸው ቅድሚያ የሚሰጡ ስለሆነ ችግራቸውን ሊፈቱ አልቻሉም።
ይባስ ብለው በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ የሀይማኖት ኩነቶች ሆን ብለው ንፁሃን ወጣቶችን በማደራጀት፤ ጥላቻ በመስበክና በመቀስቀስ ግጭት ለማስነሳት ሙከራ እያደረጉ ይገኛሉ።
ሆኖም የክልላችን ህዝብ ሰላም እና አብሮነትን ቅድሚያ የሚሰጠው እሴቱ ስለሆነና ችግሮች ቢኖሩ እንኳን ሰላማዊ እና ህጋዊ በሆነ መልኩ ለመፍታት ቁርጠኛ ስለሆነ ይህ የእኩይ ፍላጎቱና ሴራ ሊሳካ አልቻለም።
ስለሆነም እነዚህ ቡድኖች ችግሮቻቸውን ሰላማዊ እና ህጋዊ በሆነ አግባብ እንዲፈቱ በታጋሽነት እና በሆደ ሰፊነት ከፍተኛ ጥረት ቢያደርግም እነዚህ አካላት ከእኩይ ተግባራቸው ሊታቀቡ ባለመቻላቸው መንግስት ሰላምና ህግ የማስከበር ኃላፊነቱን ግዳታ ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ይገልጻል።
መላው ህዝባችን እንዲያውቀው የምንፈልገው በነዚህ ቡድኖች መካከል ያለው ልዩነት ምንም በህግ አግባብ ብቻ መፈታት እንደለበት እና መንግስት ህግን ለማስፈፀም ከመቼው በላይ የተሻለ ቁመና ላይ ያለ መሆኑን ነው።
በመሆኑም የህዝባችን ሰላምና ደህንነት ተጠብቆ እንዲቀጥል ሁሉም ህብረተሰብ ኃላፊነት እንዲወስድና ከቤተሰብ ጀምሮ ስለ ሰላም እንዲመካከርና እንዲጠብቅ በአጽንኦት እናሳስባለን።
በመጨረሻም በሰላማዊ ሰልፍ ይሁን በሌላ መልኩ ሰላም ለማደፍረስ የሚሞክር ሃይል ካለ ህዝቡ እንዲያወግዝና የህዝባችንን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ሲባል የፀጥታ ሃይሉ በጠንቀቅ ላይ ያለ መሆኑን እየገለፅን ከዚህ ሁኔታ ውጪ ለሚፈጠር ማንኛውም ክስተት የፀጥታ ምክር ቤቱ ኃላፊነት የማይወስድ መሆኑን እንገልፃለን።
ሰላም ለሁላችን ሁላችንም ለሰላም ዘብ እንቁም !!
የሀረሪ ክልላዊ መንግስት
የፀጥታ ምክር ቤት