የማህበረሰቡ ትብብር ለኮሪደር ልማቱ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል-አቶ ሙክታር ሳሊህ

ሀረር ጥቅምት 10/2017(ሀኮመኮ):-ማህበረሰቡ እያደረገው ያለው ትብብር ለኮርደር ልማቱ ምቹ ሁኔታን መፍጠሩን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር መዓረግ የሀረሪ ክልል ከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ቢሮ ሀላፊ አቶ ሙክታር ሳሊህ ገለፁ።

በሀረሪ ክልል በሚገኙ ወረዳዎች ገቢራዊ እየሆነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት አፈፃፀም በዛሬው ዕለት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር መዓረግ የሀረሪ ክልል ከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ቢሮ ሀላፊ አቶ ሙክታር ሳሊህ በውይይቱ ላይ እንደገለፁት በሁሉም ወረዳዎች የኮሪደር ልማቱ የወሰን ማስከበር ስራ በጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ማህበረሰቡ የኮሪደር ልማቱ የሚያስገኛቸውን ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ፋይዳዎች መገንዘቡን ተከትሎ ለልማቱ አስፈላጊውን ትብብር እያደረገ እንደሚገኝም ገልፀዋል።

በተለይ ማህበረሰቡ የኮሪደር ልማቱ የሚነካቸውን አጥር እና ቤቶች በገዛ ፈቃዱ በራሱ ማንሳት መቻሉ ለስራው ምቹ ሁኔታን መፍጠሩን ገልፀዋል።

አክለውም የወሰን ማስከበር ስራ በተሰራባቸው አካባቢዎች ወደ ስራ መግባት እንደሚገባ እና የተቀሩ የወሰን ማስከበር ስራዎች በቀጣዩ ሳምንት እንዲጠናቀቁ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።

የኮሪደር ልማት ስራውን በ 3 ወራት ለማከናወን ዕቅድ ተይዞ ወደ ስራ መገባቱን በማስታወስ ስራውን በምሽት ጭምር በማከናወን ከተያዘለት ጊዜ ቀደም ብሎ እንዲጠናቀቅ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ አቶ ሙክታር ሳሊህ ገልፀዋል።

Leave a Comment

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው

Scroll to Top