የፕላን ሚኒስትሯ በሀረሪ ክልል እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎችን ተዘዋውረው ተመለከቱ

የፕላን ሚኒስትሯ በሀረሪ ክልል እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎችን ተዘዋውረው ተመለከቱ

ሀረር ጥቅምት 2/2017(ሀክመኮ):- የኢፌድሪ ፕላን ሚኒስትር ዶክተር ፍፁም አሰፋ በሀረሪ ክልል እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

ሚኒስትሯ ከሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ጋር በመሆን ነው በክልሉ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎችን ተዘዋውረው የተመለከቱት።

በክልሉ እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት፣ የኢኮ ፓርክ፣ የአርሶ አደሮች ምርት መሸጫ ማዕከል፣ የአረንጓዴ ልማት እና ሌሎች በክልሉ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎች ላይ ነው የመስክ ምልከታውን ያደረጉት ።

የኢፌድሪ ፕላን ሚኒስትር ዶክተር ፍፁም አሰፋ በመስክ ምልከታው ላይ በክልሉ አበረታች የልማት ስራዎች መሆኑን መመልከታቸውን ገልፀዋል።

ሀረር የቱሪዝም መዳረሻ ከሆነ አካባቢዎች አንዱ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሯ በከተማው የተገነባው የጅብ ትርዒት ማሳያ የኢኮ ፓርክ የክልሉን የቱሪዝም አቅም የሚያጎለብት ስለመሆኑ ገልፀዋል።

በሌላ በኩል በከተማው እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት እና የአረንጓዴ ልማት ስራ ከተማዋን ለኑሮ የተመቸች ብሎም በቱሪስቶች ተመራጭ ከተማ እንድትሆን የሚያግዝ መሆኑን አስረድተዋል።

ሚኒስትሯ በክልሉ እየተገነባ የሚገኘው የአርሶ አደር ምርት መሸጫ ማዕከልን የተመለከቱ ሲሆን ማዕከሉ አምራቹን ከሸማቹ ጋር በማገናኘት ማህበረሰቡ የፈለገውን ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ ያስችላል ብለዋል።

በማዕከሉ የሚቀርቡ ምርቶች የኑሮ ውድነቱን ከማረጋጋት አንፃር ፋይዳቸው የጎላ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

ካሁን ቀደም በአገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ አካባቢዎች የተጀመረው የቅዳሜ ገበያ አበረታች ውጤት የተመዘገበበት መሆኑን በመጠቆም የቅዳሜ ገበያን ደረጃውን በጠበቀ መልኩ የማስፋት ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

በክልሉ የተገነባው የአርሶ አደር ምርት መሸጫ ማዕከልም የቅዳሜ ገበያውን ከመንገዶች ላይ በማንሳት በተደራጀ ሁኔታ ለማከናውን እንደሚያስችል ጠቁመዋል።

በመስክ ምልከታው የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪን ጨምሮ የክልሉ የፓርቲ እና የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።

Leave a Comment

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው

Scroll to Top